ሃልማርክ ኮሌጅ የስርዓተ-ትምህርት ግምገማ ወርክሾፕ በጎንደር ኦሎምፒክ ሆቴል አካሄደ
ሃልማርክ ኮሌጅ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች እየተቋቋመ የሚገኝ ኮሌጅ ሲሆን በሶስት የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ማለትም በንግድ አስተዳደር (Business Administration)፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት (Project Management) እና በገበያ አሰተዳደር (Marketing Management) በጎንደር ከተማ የማስተማር ፈቃድ ለማግኘት የስርዓተ ትምህርት ግምገማ ህዳር 03/2015 ዓ.ም በኦሎምፒክ ሆቴል አካሂዷል። በ ወርክሾፑ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የውጭና የውስጥ ገምገሚዎች ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመገኘት ገንቢ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በወርክሾፑ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮሌጁ ጊዜያዊ ዲን ፕሮፌሰር አሰግድ ደምሴ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚታየውን ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታትና በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳደሪ መሆን የሚችሉ የሰው ኃይልን ለማፍራት አልሞ ስማርት ኢንተርናሽናል ኮሌጁ እንደተቋቋመ ተናግረዋል። ኮሌጁ ለጊዜው በ 2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች የማስተማር ፍቃድ ለማግኘት እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ ገልጸው ፤ በውስጡ ከያዛቸው ልምድ ካላቸው ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች አንፃር በ3ኛ ዲግሪም መጀመር እንደሚያስችለውና ይህንንም በቅርቡ እውን እንደሚያደርገው ገልፀዋል።
ስለሃልማርክ ኮሌጁ አጠቃላይ ገለፃ ያደረጉት ደግሞ ዶ/ር አስማማው ጥላሁን ሲሆኑ በገላፃቸውም ኮሌጁ በጎንደር ከተማ የሚታየውን የከፍተኛ ት/ት ተቋም እጥረት ለመፍታት ጥሩ አማራጭ እንደሚሆንና ኮሌጁ ከየትኛውም ተቋም በላይ በቋሚ መምህራን የተደራጀ መሆኑንና ለዚህም 2 ሙሉ ፕሮፌሰሮችን ፣ 1 ተባባሪ ፕሮፌሰርና 3 የ3ኛ ዲግሪ ባለቤቶችን መያዙ ልዩ እንደሚያደገው ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ በዘመናዊ ቁሳቁሶች የተደራጀ ፤ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አለም አቀፍ ጆርናሎችን በአባልነት የተቀላቀለ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
በወርክሾፑ ላይ የኮሌጁ ድህረ ገፅ (www.hallmarkcollege.edu.et) ደግሞ በአቶ አበበ አለሙ በኩል ተሰርቶ የቀረበ ሲሆን ድህረ ገፁ ስለ ኮሌጁ አጠቃላይ መረጃን፣ ተማሪዎች በየትኛውም ቦታ ሆነው በኦንላይን መመዝገብ የሚችሉበትንና የኦንላይን ትምህርትን ማስጀመር የሚችልበትን (e-learning) አሟልቶ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በወርክሾፑ ላይ በዶ/ር ዋሴ ጌታሁን በኩል 3ቱ ስርዓተ ትምህርቶች ቀርበው በውጭ ገምጋሚዎችና በተሳታፊዎች በኩል አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የወርክሾፑን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ኃላፊ አቶ አወቀ አስፈሬ ሲሆኑ በንግግራቸውም ከፍተኛ ኃላፊነትን ወስዳችሁ ፤ መደበኛ ስራችሁን ለቃችሁ ፤ ጎንደር ከተማ ታሪኳን የሚመጥን ልዩ የሆነ ኮሌጁ ያስፈልጋታል ብላችሁ እንቅስቃሴ በመጀመራችሁ እንደ መንግስት ደስተኞች ነን ፤ ነገር ግን ጥራት ላይ በምንም መልኩ እንዳትደረደሩ የኮሌጁን መስራች አባላት አደራ ብለዋል።








